በአውስትራሊያ በጋ ወቅት ራስን ለመጠበቅና ቀዝቀዝ ለማለት አምስት ፍንጮች

Loving couple at the beach

tips to keep safe and cool during an Australian summer - Getty Credit: andresr/Getty Images

Get the SBS Audio app

Other ways to listen

ዓመቱን በሙሉ ሰውነትዎ የሚሻውን ማድመጡ ጠቃሚ ነው፤ ከቶውንም በገረረ የአየር ንብረት ወቅት በጣሙን ወሳኝ ይሆናል። የአውስትራሊያን በጋ ለመርታት አስፈላጊ ፍንጮችን እነሆ።


አንኳሮች
  • በበጋ ወቅት ውኃ ወይም ፈሳሾችን መጠጣት ወሳኝ ነው
  • ሁሌም ወደ ደጅ ሲወጡ SPF 50 ወይም ከዚያ ከፍ ያለ የፀሐይ ጨረር መከላከያ ቅባት ይጠቀሙ
  • ሁሌም ከቤት ወደ ደጅ ከመውጣትዎ በፊት የአልትራ ቫዮሌት መጠንን ያረጋግጡ
“ሰውነታችን በመልካም ሁኔታ የታነፀ መሺን ነው። የሰውነታችንን ሙቀት መጠን ለማስተካከል በሚያግዝ ቴርሞስታት የተገነባ ነው” ሲሉ የሲድኒ ጠቅላላ ሐኪም አንጀሊካ ስኮት አተያያቸውን ያጋራሉ።

ሰውነት ሙቀት ሲገጥመው ተገቢውን የሙቀት መጠንን ጠብቆ ለመቆየት በተለያዩ መንገዶች ግብረ ምላሽ ይሰጣል።

ለሙቀት አካላዊ ምላሽ

የአየር ንብረቱ ሞቃት ሲሆን፤ ሰውነታችን የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማል። ዋነኛው ላብ እንደሆነ ሐኪም ስኮት ያስረዳሉ።
ሙቀት ሲሆን፤ የላብ ዕጢዎች ውኃ ወይም ላብን ይረጫሉ፤ ያኔ ከቆዳችን ላይ ይተናል። ሙቀቱን ለመሸሽና ሰውነታችን ቀዝቀዝ እንዲል ያግዛል።
ሐኪም አንጀሊካ ስኮት
ከማላብ በተጨማሪም ቆዳችን ውስጥ የደም ስሮችን እንዲሁ በማስፋት ወይም በመከፈት በቆዳችን በኩል ሙቀት ለመልቀቅ ያስችሉናል።

“ለዚያም ነው ሙቀት ሲሆን ቆዳችን የቀላ ወይም የከሰለ የሚመስለው" በማለት አክለዋል።

ሐኪም ስኮት በሞቃት አየር ንብረት ወቅት የሰውነታችንን 'የኃይል መተላለፍ' ሂደት ክስተት ያነሳሉ።

“ሰውነትዎ ሙቀቱን ከዋነኛው አካል ወደ ሌሎች አካላት ሊገፋ ይሞክራል። ይህም ሲሆን ክንዶችዎ፣ እጆችዎና እግሮችዎን ያልብዎታል” በማለት።
ሙቀት ከላብና የቆዳ መቅላት ወይም መክሰል ባሻገር ፈጣንና የተቆራረጠ አተነፋፈስን እንደሚያስከትልም ሐኪም ስኮት ያስረዳሉ። ሞቃት አየር ከ 'መደበኛ' አየር መጠን ከበድ እንደሚልም ጭምር።

በሞቃት አየር ንብረት ወቅት የውሾችን በማለክለክ ራሳቸውን የማቀዝቀዣ መንገድ በማነፃፃሪያነት ያመላክታሉ፤ "እኛ ሰዎችም እንዲሁ ሙቀትን ለመክላት ስንሞክር በፍጥነት እንተነፍሳለን" ሲሉ።

ሙቀት እኒህን የተዘወተሩ ምልክቶች ሲያመጣ፤ የገረረ የአየር ንብረት ግና ከሙቀት ጋር የተያያዙ ሕመሞችንና ከቅጥ ያለፈ ሙቀት ያስከትላል ሲሉም ያስጠነቅቃሉ።
ከመጠን ያለፈ ሙቀት ለአስቸኳይ ሕክምና ዳራጊ ነው። የሙቀት ድካምን በተመለከተ ምልክቶቹን ማወቅ ጠቃሚ ነው። በብዛት ማላብ፣ መድከም፣ ማቅለሽለሽ፣ መፍዘዝ፣ ደካማ የልብ ምት ወይም ፈጥኖ መትቶ ዝቅ የሚል የልብ ምት፣ ግር መሰኘትና ደረቅ ቆዳ። ዐልፎም ራስን የመሳት ምልክቶች።
ሐኪም አንጀሊካ ስኮት
ብሔራዊ የቆዳ ካንሰር ኮሚቴ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አን ከስት፤ ሰዎች ለብርቱ ሞቃታማ በጋ እንዲሰናዱ ምክረ ሃሳብ ይቸራሉ።

“ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለአውስትራሊያውያን ከቤት ውጪ ጊዜን ማሳለፍ በብርቱ አዋኪ ነው የሚሆነው። የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ እንደ ደን ቃጠሎዎችና ጎርፎች አሉብን። ገጥሞን ያለውም የከረረ አየር ንብረት ነው” በማለት።

ፍንጮች ደኅነንትን ጠብቆና ቀዝቀዝ ብሎ ለመቆየት

በበጋ ቀናት ከመጠን ያለፈ ሙቀትን ወይም ከሙቀት ጋር የተያያዙ ሕመሞችን ለማስወገድ፤ ሐኪም ስኮት የሚከተሉትን ምክሮች አስተውሎ መከተል እንደሚያሻ ይመክራሉ፤

1. ውኃ ወይም ፈሳሾችን ይጠጡ 

“ሰውነትዎ ያጣቸውን ፈሳሾች በውኃ ይተኩ፤ እናም በየዕለቱ ውኃ ይጠጡ። ሁሌም የጠርሙስ ውኃ መያዝ ጠቃሚ ነው።

“አንዳንዴ በቂ ውኃ የጠጣን አድርገን እናስባለን፣ እንደ እውነቱ ከሆነ ግና በቂ ውኃ አልጠጣንም። መጠጣት የሚገባን በቀን ሶስት ሊትር ውኃ ነው።”

ውኃ ምንጊዜም በሞቃት በጋ ቀን የሚጠጣ ፈሳሽ ሲሆን፤ ሐኪም ስኮት የአልኮል መጠጦችና ሶዳዎችን መመጠጣትን አስመልክተው ያስጠነቅቃሉ።

“ሰዎች በአንድ ቆርቆሮ ሶዳ ጥማቸውን የቆረጡ መስሎ ይታሰባቸዋል፤ ይሁንና ሶዳ ከፍተኛ ስኳር ስላለው ጥምን ለመቁረጥ ተመራጭ አይደለም።

“የሚጠጡት ፈሳሽ የተለየ ጣዕም ያለው እንዲሆን የሚሹ ከሆነ ለሶዳ አማራጭ ሆነው... የሚያሻዎትን ፈሳሾች በመተካት የስፖርት መጠጦች ያግዛሉ”

2. የተወሰኑ ምግቦችን ያስወግዱ 

“በሞቃት አየር ንብረት ወቅት ፍራፍሬዎችና ቅጠላ ቅጠሎች ለመመገብ ማለፊያ ናቸው፤ በተለይም እንደ ሃብሃብና ዱባ የመሰሉ ውኃ አዘሎች”

ሐኪም ስኮት ከከባድና ስብ ምግቦች ይልቅ ቀላልና ሳያውኩ የሚደቅቁ ምግቦችን መምረጥ ቀዝቀዝ ያለ የሰውነት ሙቀት መጠንን ጠብቆ እንደሚያቆይ ይናገራሉ።

“ከባድ ምግቦችና ከፍተኛ ስኳር ያለው ምግብ ሰውነትዎ ደክሞ እንዲሠራና የሰውነትዎ ሙቀት መጠን እንዲንር ያደርጋሉ።”
Cheerful woman gardening in backyard
Stay hydrated throughout the day as a critical preventive measure against heat exhaustion. Credit: The Good Brigade/Getty Images
3. እኒህን አምስት ነገሮች ልብ ይበሉ፤ ተከላካይ ልብሶች፣ ባርኔጣ፣ መነፅር፣ የፀሐይ ጨረር መከላከያ ቅባትና ጥላ። 

እንደ ዋና ኃላፊዋ ኢማ ግላሰንበሪ፤ ከፀሐይና አልትራ ቫዮሌት ጨረር የሚከላከሉ አምስት ጠቃሚ ነገሮች አሉ።

“ሁሉንም አምስት የፀሐይ መከላከያ፤ ተከላካይ ልብሶች፣ ጠርዘ ሰፊ ባርኔጣ፣ የፀሐይ መነፅሮች፣ የፀሐይ ጨረር መከላከያ ቅባትና ጥላን ለተጨማሪ መከላከያ ይጠቀሙ” ሲሉ አተያያቸውን ያጋራሉ።

ወ/ሮ ግላሰንበሪ፤ ወደ ባሕር ዳርቻ ሲኬድ ወይም የውኃ እንቅስቃሴዎች ሲደረግ የፀሐይ መከላከያ መጠቀም የተለመደ የመሆኑን ያህል፤ በሰዎች የዕለት ተዕለት ክንውኖች ጋርም ተዛንቆ ሊዋደድ ይገባዋል ይላሉ።

“ሰንስማርት ቪክቶሪያ 'ካንሰር እንዲዝልቅ አይፍቀዱለት' የሚል አንድ አዲስ ዘመቻ በይፋ ጀምሯል። የቆዳ ካንሰርን ለመከላከል የፀሐይ መከላከያን የመጠቀም ጠቃሚነትን አስራጭ ነው።

“የፈለገውን ዓይነት እንቅስቃሴ ያድርጉ ያ ጉዳይ አይደለም። ውሻዎን ይዘው እየተጓዙ ይሁን፣ የጓሮ እርሻዎን እየኮተኮቱ፣ ጓሮ ሆነው ልጆችን እየጠበቁ ይሁን ወይም ውጪ እየተጓዙ፤ ራስዎን ይሸፍኑ።”

4. እንቅስቃሴዎችዎን ከቀኑ የአየር ንብረት አልትራ ቫዮሌት መጠኖች መሠረት ያድርጉ 

ሐኪም ስኮት፤ ወደ ውጪ ከመውታትዎ ወይም አካላዊ እንቅስቃሴ ከማድረግዎ በፊት የዕለቱን የአየር ንብረት ትንበያ እንዲያጣሩ ምክረ ሃሳባቸውን ይለግሳሉ።

“የአየር ንብረቱን ካጣሩ ስንዱ ነዎት ማለት ነው።

“የሙቀት መጠኑ ከፍ ያለ መሆኑን ካወቁ፤ የውጪ እንቅስቃሴዎችዎን በተቻለ መጠን ያስወግዱ። በጥቅሉ፤ ከእኩለ ቀን እስከ ከቀትር በኋላ 3 pm የዕለቱ በጣም ሞቃት ጊዜያት የሚሆኑበት ነውና በእዚያን ወቅት ወደ ውጪ ላለመውታት ይጣሩ።”

ፕሮፌሰር ከስትም እንዲሁ በማከል፤ ወደ ውጪ ከመውጣትዎ በፊት የዕለቱን አልትራ ቫዮሌት መጠን ማጣራት ጠቃሚ ነው ይላሉ።
በተከታታይ ለከፍተኛ አልትራ ቫዮሌት ጨረር መጋለጥ ለቆዳ ካንሰር ዋነኛ ምክንያት ነው።

ፕሮፌሰር ከስት “አውስትራሊያ ውስጥ ይበልጥ ብርቱ የሆነ አልትራ ቫዮሌት ጨረር ተጋላጭነት ያገኘናል፤ አውሮፓ ካሉቱ እጥፍ ያህል አውስትራሊያና ኒውዝላንድ ውስጥ ስለምን የቆዳ ካንሰር መጠን ከፍተኛ እንደሆነ አስረጂ ነው ብለን እናስባለን” ይላሉ።

አልትራ ቫዮሌት ጨረር ስለማይታይ ወይም ስለማይሰማን የቀኑን ሞቃትነት በእዚያ ይወሰናል ማለት እንዳልሆነም አበክረው ያሳስባሉ።

“በበጋ ወራት አውስትራሊያ ውስጥ አብዛኛውዎቹ ሥፍራዎች አልትራ ቫዮሌት ከ12 እስከ 14 ሲደርስ መለኪያ አላቸው፤ በደቡባዊ አውሮፓ ሜዲትራኛን አካባቢ ግና የአልትራ ቫዮሌት መጠን ከፍ ብሎ የሚደርሰው እስከ ስምንት ነው።

“ቀዝቀዝ ያለ ቀንም ቢሆን፤ የአልትራ ቫዮሌት መጠን ከፍ ያለ ይሆናል። መጠነኛ ነፋሻነት በአካባቢው ካለ ውጪ ቀዝቀዝ የማለት ስሜት ሊኖር ይችላል ግ ና የአልትራ ቫዮሌት መጠን በጣሙን ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል።”
Asian mother applying sunscreen lotion to protect her daughter's face before exercise while setting on floor in the park at outdoors
Most places in Australia have a UV index that peaks at around 12 to 14 in the summer months Credit: Six_Characters/Getty Images
5. አቅምዎን ይወቁ ከንቱ ልፋትን ያስወግዱ 

እንደ ሐኪም ስኮት አባባል፤ በቀላሉ ድካም የሚሰማዎት ከሆነ፣ በሞቃት አየር ንብረት ረዘም ላለ ጊዜ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ካልቻሉ ወይም ጤነኝነት ካልተሰማዎ፤ ሰውነትዎን ያሳርፉና እርዳታን ይጠይቁ። የሰውነትዎን አቅም ይወቁ።

“ይሁንና ገላዎን በፀሓይ ማሞቅ፣ የእግር ጉዞ ማድረግ ወይም ውጪ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግን በጣሙን የሚያፈቅሩ ከሆነ፤ ሰውነትዎ ለሚያስተላልፍልዎ መልዕክቶች በጣሙን ትኩረት ይስጡ። ሰውነትዎን እስከ የመጨረሻ አቅሙ እየገፉ መሆንዎ ከተሰማዎ፤ አረፍ በማለት ሰውነትዎን ቀአቀአ ያድርጉ፤ ጥምዎን ይቁረጡ።”

ወ/ሮ ግላሰንበሪ በሐኪም ስኮት አባባል በመስማማት ሲያክሉ “የምንኖረው ውብ የውጪ ሥፍራዎች ባሏት ድንቅ አገር ላይ ነው፤ ሆኖም ይህ አብሮ ያለው ለቆዳ ካንሰር ዳራጊ ከሆነ ብርቱ የአልትራ ቫዮሌት መጠን ጋር ነው። እናም፤ ስዎች ውጪ ወጥተው እንዲደሰቱ እንሻለን፤ ይሁንና የአልትራ ቫዮሌት መጠን ሶስት ሲደርስ እንዲሸፈኑ እንፈልጋለን” ብለዋል።

ስለ አካባቢዎ ዕለታዊ የአልትራ ቫዮሌት መጠኖች ይበልጥ መረዳት ካሹ ይጫኑ።

የአውስትራሊያ ጨረር መከላከልና ኑክሊየር ጥንቃቄ አጄንሲን ሊጎበኙ ይችላሉ።

Share